Ubah Abdusalam seid
እኛ የኢትዮጵያ ሙስሊም ወጣቶች “አህባሽ”ን የምንታገለው አንጃው ከኛ የተለየ አመለካከትና የእምነት ፍልስፍና ስለያዘ አይደለም፡፡ የትግላችን መነሾዎች
- አንጃው የሀገራችን ሙስሊሞች ሁሉ የጋራ ተወካይና መንፈሳዊ መሪ መሆኑ የሚታመንለትን የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ም/ቤት በሞኖፖል በመቆጣጠሩ በኑፋቄና በጥመት የተወገዘውን የእምነት ፍልስፍናውን በመላው ኢትዮጵያ የሚሰራጭበት እድል በመፈጠሩ
- አንጃው ባለው የፅንፈኝነት ባህሪ ከርሱ ጋር የማይጣጣሙትን ሁሉ “ከፍራችኋል” (ከኢስላም ወጥታችኋል ) እያለ በወንድማማቾች መካከል የጥላቻና የሽብር መርዝ ሲዘራ እንደነበረ በስፋት ስለሚታወቅና “ይህንን ድርጊት በሀገራችን መድገሙ አይቀርም” ብለን ስለሰጋን
- አሜሪካ “የወሃቢያን እንቅስቃሴ ለመቆጣጠር” በሚል ሽፋን በሙስሊሞች ላይ ለከፈተችው ኢ-ፍትሐዊ ዘመቻ ይህን በኑፋቄና በጥመት የተወገዘ የአህባሽ አንጃ ፊታውራሪ አድርጋ ማሳለፏ በበቂ ማስረጃዎች በመረጋገጡ
- የአንጃው ጽንፈኛ አመለካከቶች በሙስሊሙና በሌላ ሀይማኖት ተከታዮች መካከል ለረጅም ዘመናት ጸንቶ የቆየውን የመተባበርና የመቻቻል ባህል ያደፈርሳል ብለን ስለሰጋን እና ሌሎችም ምክንያቶች ናቸው፡
- በመሆኑም ይህ አንጃ በእምነታችንና በሰላማችን ላይ የደቀነውን አደጋ ለመቀልበስ በምንችለው መንገድ ሁሉ ለመታገል ቆርጠን ተነስተናል፡፡ ትግላችንን የምናካሄደው በህጋዊና ሰላማዊ መንገድ ብቻ ነው፡፡ ግባችንም በሀገራችን ህገ መንግስት የተረጋገጠልንን የእምነት ነጻነት መብታችንን ማረጋገጥ ነው፡፡
የእስከዛሬው ትግላችን የአንጃውን የኋላ ታሪክ፤ በኑፋቄ የተሞሉ የእምነት ፍልስፋናዎቹን፤ የጽንፈኝነት ባህሪውን፤ የስርጭት አድማሱን፤ ወዘተ… በማጋለጥና ለወንድሞቻችንና እህቶቻችን በማሳወቅ ላይ ያተኮረ ነው፡፡ በዚህ ሳምንት ያየናቸው አንዳንድ ድርጊቶች ግን ትግላችን ማስፋት እንዳለብን የሚጠቁሙ ናቸው፡፡ ለዚህም ልዩ ልዩ ስልቶችን መከተል ያስፈልጋል፡፡ በዚህ መሰረትም የሚከተሉት የትግል ስልቶችን መንደፍ አስፈላጊ ሆኖ ታይቶኛል፡፡
1. መንግስታትን በሚመለከት
1.1. የኢትዮጵያ መንግስት አካላት (ባለስልጣኖችም ሆኑ ተቋማት) ስለ አህባሽ ምንነት በቂ መረጃ ያላቸው አይመስለኝም፡፡ የአንጃው የእምነት ፍልስፍና አጠቃላዩ የዓለም ሙስሊም ህብረተሰብ ከሚከተላቸው የእስልምና አስተምህሮዎች የቱን ያህል እንደሚራራቅ በደንብ አያዉቁትም፡፡ ስለዚህ አህባሽ በብቸኝነት በኢትዮጵያ ውስጥ ትምህርቱን እንዲሰጥ መፍቀድ ማለት “እስከዛሬ ድረስ የምትከተሉትን እምነት ቀይሩ” የማለት ያህል እንደሆነ ለሁሉም የመንግስት አካላት በምንችለው መንገድ ሁሉ ማሳወቅ አለብን፡፡
1.2. ከዓለም አቀፍ ፖሊሲ ትንተናው በመነሳት “አህባሽ”ን ለኢትዮጵያ ሙስሊሞች መሪነት ለመረጠው የአሜሪካ መንግስት ትንተናው የተመሰረተው በተሳሳተ ግምገማ ላይ እንደሆነ በሚቻለው መንገድ ሁሉ ማሳወቅ አለብን፡፡ (ለምሳሌ የአሜሪካ መንግስት እንደሚለው የአክራሪነትና እና የጽንፈኝነት አመለካከቶች በሀገራችን ውስጥ መሰረት እንደሌላቸው ማሳወቅ አለብን)፡፡
1.3. “ሽብርተኝነት”ን ለመዋጋት መፍትሔው በቀድሞው የሊባኖስ ጠቅላይ ሚኒስትር ግድያ ከተወነጀሉት የሽብር ግበረ-ሃይሎች አንዱ የሆነውን “አህባሽን” ለኢትዮጵያ ሙስሊሞች መሪነት መምረጥ ሳይሆን ሽብርተኝት በኢስላም ሃይማኖታዊ መሰረት እንደሌለው የሚያውቁትን ሙስሊሞች በጋራ ማንቀሳቀስ እንደሆነ ማስረዳት አለብን፡፡ (ኢስላምን አስታከው ድብቅ አጀንዳቸውን ማራመድ የሚፈልጉ ሃይሎች ካሉ ሙስሊሙ ራሱ ሊቆጣጠራቸው ይችላል)፡፡
2. አህባሾችን በተመለከተ
2.1. አህባሾች በአራት ክፍል እንደሚመደቡ መታወቅ አለበት፡፡ እነርሱም
ሀ/. ዓለም አቀፍ አህባሾች ፡- እነዚህኛዎቹ በሀገራችን ውስጥ በብዛት የሉም፡፡ ሆኖም በማእከሎቻቸው በአስተማሪነት ይመደባሉ፡፡ እነዚህ ሰዎች በእምነት ስም በሌላው አለም (በተለይ በሊባኖስ) የለመዱትን በመርዝ የተለወሰ የጥላቻ ትምህርት በሀገራችን እንዲያስፋፉ የሚፈቅድላቸው የህግ አንቀጽ የለም፡፡ (ሰላማዊ ስብከት እንጂ “እገሌ ካፊር ነው በሉ”፤ “ከወሃቢ ጋር ቡና አትጠጡ፤ ምሳ አትብሉ፤ ትከፍራላችሁ” እያሉ እንዲያስተምሩ የሚፈቅድላቸው የህግ አንቀጽ የለም)፡፡ ስለዚህ የጥላቻ ዘመቻቸውን ማጋለጥና በህጋዊ መንገድ መታገል ይገባል፡፡ (እነ ዶ/ር ዛኪርን በ”ኩፍር” የወነጀሉት እነዚህ አለም አቀፍ አህባሾች ናቸው፡፡)
ለ/. በዜግነት ኢትዮጵያዊ የሆኑ ጽንፈኛ አህባሾች፡- እነዚህኛዎቹን በኢስላማዊ አስተምህሮች እየተከራከሩ መመለሱ በእጅጉ ይከብዳል፡፡ ስለዚህ ብዙም ባናተኩርባቸው ይሻላል፡፡
ሐ/. ኢትዮጵያዊ የሆኑ ለዘብተኛ አህባሾች፡- እነዚህኛዎቹ ከሌላው ሙስሊም ጋር ይቀራረባሉ፡፡ ከኛ ጋር በጀመኣ አንድ መስጊድ ሊሰግዱም ይችላሉ፡፡ (በ”ለ” የተጠቀሱት ግን ጁምዓ እንኳ ለብቻቸው ካልሆነ በስተቀር ከኛ ጋር አይሰግዱም)፡፡ ስለዚህ በዚህ ስር የሚጠቃሉትን የአህባሽ ሰዎች እስከምንችለው ድረስ መምከርና ለመመለስ ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል፡፡
መ/ “አኩራፊ አህባሾች”፡- እነዚህኛዎቹ በኛው አያያዝ ተናደው ወደ አህባሽ የተጠጉ ናቸው፡፡ ለምሳሌ አንዳንድ የሀገራችን ሙስሊሞች ከባህል የወረሷቸውና በእስልምና ተቀባይነት የሌላቸው በርካታ ልማዶች ይታይባቸዋል፡፡ እነዚህን ወገኖች ዳዒዎች በለዘብታ ቃላት ማስተማር ሲገባቸው በከረረ ቃላትና ወቀሳ (አንዳንዴም በስድብ) ይወርዱባቸዋል (“ሙሽሪክ” ብሎ የሚወነጅላቸው ሰውም አለ)፡፡ በመሆኑም እነዚህ ወገኖች ያኮርፉና ወደ “አህባሽ” ጎራ ይገባሉ፡፡ ስለዚህ ዳዒዎች ማስተካከል ያለባቸውን ግድፈቶች ማረምና ወገኖቻችንን ማስተማር አለባቸው፡፡
2.2. በማንኛውም ወቅት የአህባሽ ጎራ ተከታይ ከሆነ ሰው ጋር ከቃላትና ከጽሁፍ የዘለለ ክርክር ማድረግ የለብንም፡፡ (ለግጭት በሚጋብዝ ሁኔታ መከራከር አይገባንም)፡፡
2.3. የአህባሽ ተከታዮችን እራሳቸው ካልፈለጉ በስተቀር ከማህበራዊ ኑሮ ማግለል አይገባም፡፡
3. የሀገራችን ሙስሊሞችን በሚመለከት
3.1. የሀገራችን ህዝብ ሙስሊም ስለ አህባሽ በቂ መረጃ እንዲያገኝ ማድረግ አለብን፡፡ ለዚህም አሁን ከጀመርነው የኢንተርኔት መስኮት በተጨማሪ ሌሎች መንገዶችንም መጠቀም አለብን፡፡
3.2. የሀገራችን ምሁራን በትግላችን እንዲሳተፉ መጋበዝ አለብን፡፡ (ለምሳሌ ከዚህ ቀደም በተክፊር ወል-ሂጅራ በተበላው ጠማማ ቡድን ላይ በርካታ መጽሀፍት እንደተጻፉት ሁሉ በአህባሽም ላይ ተመሳሳይ ድርሰቶች መጻፍ አለባቸው፡፡)
3.3. ታዋቂ ግለሰቦችም ድምጻቸውን ማሰማት እንዲችሉ መቀስቀስ ይገባል፡፡
3.4. የሙስሊም ጋዜጦቻችን የጀመሩትን አህባሽን የማጋለጥ ዘመቻ አጠናከረው ሊቀጥሉበት ይገባል፡፡
4. ከሀገራችን ውጭ ያለውን ህዝበ ሙስሊም በተመለከተ
4.1. በዲያስፖራ ያሉት ኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞች በሰላማዊና ህጋዊ ትግላችን እንዲሳተፉ መቀስቀስ አለብን፡፡
4.2. ይህ ጉዳይ የኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞች ጉዳይ በመሆኑ ሌሎች መንግስታትና የውጪ ሀገር ዜጎች በቀጥታ የሚሳተፉበት ምክንያት የለም፡፡ ሆኖም አህባሽ በዓለም ዙሪያ ተሰራጭቶ ሙስሊሞችን እየበጠበጠ ያለ ቡድን በመሆኑ ስለ አንጃው ድብቅ ታሪኮችና እንቅስቃሴዎች፤ ስለእምነት ፍልስፍናው መሰረቶች፤ ስለ ማሳሳቻ ስልቶቹ፤ የዓለም ሙስሊም ምሁራን የሰጧቸውን ፈትዋዎ፤ የአንጃውን እንቅስቃሴ ለመገደብ የወሰዷቸውን እርምጃዎች ወዘተ… በመሳሰሉት ላይ ሃሳባቸውን በማጋራት ለመተባበር ከፈለጉ በደስታ እንቀበላቸዋለን፡፡
ይህ የትግል ስልት ለውይይት የቀረበ ነው፡፡ ማንኛውም ሙስሊም አባል ሃሳቡን ሊሰጥበት ይችላል፡፡
አላህ ይርዳን፡፡ ወሰላሙ ዓሌይኩም ወራሕመቱላህ
ኡባህ አብዱሰላም
No comments:
Post a Comment