Wednesday, May 9, 2012

“አህባሽ” እና የሙስሊሙ አንድነት

March 10, 2012 at 6:00pm ·

በዚህ ጽሁፍ አህባሽ አደጋ በደቀነበት የሙስሊሙ አንድነት ዙሪያ ቆይታ እናደርጋለን፡፡

አህሉ ሱንና ወል-ጀመዓ
   እኛ ሙስሊሞች የምንከተለው ዲን (ሀይማኖት) ኢስላም ነው፡፡ ኢስላምን የሚከተል አንድ ግለሰብ “ሙስሊም” ነው፡፡ ሁሉም ሙስሊሞች አንድ ላይ “ኡማ” ይባላሉ፡፡ በሌላ በኩል እኛ አሁን ያለንበት መንገድ ጥንት ከነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ) እና ከሰሀባዎች ዘመን የተነሳው ቀጥተኛ ጎዳና መሆኑን ለማመልከት የሰለፍ ኡለማ “አህሉ ሱንና” (በሱንና ላይ ያሉ ህዝቦች) የሚል ቅጽል ሰጥተውናል፡፡ በተጨማሪም የአላህን ቀጥተኛ ገመድ የያዝንና በውስጣችንም ክፍፍል የሌለብን መሆኑን ለማስረዳት “አህሉል ጀመዓ” (በአንድነቱ የጸና ህዝብ) በማለት ጠርተውናል፡፡ ሁለቱ ስሞች አንድ ላይ በመጣመር አህሉ ሱንና ወል-ጀመዓ (በሱንና ላይ ያለውና ያልተከፋፈለው ህዝብ) የሚለውን መጠሪያችንን አስገኝተዋል፡፡
   እኛ ሙስሊሞች “አህሉ ሱንና” ነን፡፡ እኛ ሙስሊሞች “አህሉል ጀመዓ” ነን፡፡ አንድነት የኛ መለያ ነው፡፡ አንድነታችን ጌጣችን ነው፡፡ አንድነታችን ክብራችን ነው፡፡ ኢስላምን በጠላቶቹ ፊት ክብር ያሰጠው የሙስሊሙ አንድነት ነው፡፡ የኢስላም ጠላቶች ከጦር በላይ የሚፈሩት መሳሪያ ቢኖር የሙስሊሙ አንድነት ነው፡፡
   የዚህ ኡማ አንድነት በቀላል ልፋትና ትግል አይደለም እዚህ የደረሰው፡፡ በርካታ የ”ፊትና” ዘመናት ታልፈዋል፡፡ ሰሀባዎችና ተቢኢዮች በሺዓ እና በኸዋሪጃ ፊርቃዎች የተነጠሉትን ወገኖቻቸውን ወደ ኡማው ለመመለስ እልህ አስጨራሽ ትግል አድርገዋል፡፡ ኸሊፋዎችና ታላላቅ ኡለማዎች በየወቅቱ ይነሱ የነበሩትን የአመለካከት ልዩነቶች በዘዴ እየፈቱ የኡማውን አንድነት አስጠብቀዋል፡፡ አላህ እነዚያ ጥረቶችን ሰበብ ስላደረገ ነው አንድነታችን ተጠብቆ እዚህ የደረሰው፡፡
የአመለካከት ልዩነት በራሱ መጥፎ አይደለም
   ኢስላም ህያው ሀይማኖት ነው፡፡ ህያው የሆነ እምነት በውስጡ የአመለካከት ልዩነቶች መታየታቸው አይቀርም፡፡ ልዩነት በራሱ መጥፎ አይደለም፡፡ የአመለካከት ልዩነት በመከሰቱ ብቻ የኡማውን አንድነት ይንደዋል ማለት አይደለም፡፡ እንዲያውም አላህ በልዩነት ውስጥ ለኢስላም ውበት የሰጡ በርካታ ጸጋዎችን አጎናጽፎናል፡፡ ለምሳሌ አራቱ የፊቅሂ መዝሀቦች ጸጋዎቻችን ናቸው፡፡ ሰባቱ የቂራአት (የቁርአን ንባብ ደንብ) መንገዶችም እንዲሁ የኢስላም ውበቶች ናቸው፡፡ እነዚህ ክስተቶች ጸጋዎቻችን ሊሆኑ የቻሉት ኡለማዎች የልዩነት መንገዶች ስላላደረጓቸው ነው፡፡ ልዩነቱን ያመጡት ቀዳሚ ሰዎች በአመለካከት የተለዩትን ሰው ወደ መዝለፍና ማጥላላት አልገቡም፡፡ “እኔ ያልኩት እንጂ ሌላው ትክክል አይደለም” በሚል ስሌት “ቡራ ከረዩ” አላሉም፡፡ በልዩነታቸው ውስጥ ይከባበሩ ነበር፡፡
  ለምሳሌ አቡ ሀኒፋ፤ ማሊክ ኢብን አነስ፤ ሙሀመድ ኢብን ኢድሪስ አል-ሻፊኢ፤ አህመድ ኢብን ሀንበል አንዳቸው ለአንዳቸው ተማሪና አስተማሪ ነበሩ፡፡ እነርሱ የነበራቸው የህግ አተረጓጎም ልዩነት ነው አሁን ያሉትን አራት መዝሀቦች ያስገኘው፡፡ ታዲያ እነዚህ ኡለማ በአመለካከት ቢለያዩም በጣም ይፈቃቀሩ ነበር፡፡ እኛም ዛሬ ያለነው ሙስሊሞች አራቱንም ኢማሞች በጣም ነው የምናከበራቸው፡፡
   ከዚህ እንደምትረዱት የአመለካከት ልዩነት ሁልጊዜ የጀመዓ መነጣጠልን የሚያስከትል ተደርጎ መታየት የለበትም፡፡ በቅን ልቦና ካየነው ልዩነት ተጨማሪ ጸጋዎችንም ሊያጎናጽፈን ይችላል፡፡
 ልዩነትን በጥበብ መያዝ
   ከላይ እንደገለጽኩት የአመለካከት ልዩነት በመፈጠሩ ብቻ ወደ መነጣጠል የሚወስድ ተደርጎ መወሰድ የለበትም፡፡ ከይሲዎችና ደካማዎች ግን መጠነኛ ልዩነቶችን እያገዘፉ ትልቅ የመገንጠል ገደል ይቆፍሩበታል፡፡ የኢስላም ታሪክ የሚያስረዳው ይህንኑ ነው፡፡ አላህ ቅን ልቦና የሰጣቸው አርቆ አስተዋዮች ግን በሃሳብ መለያየቱን ብቻ ሳይሆን መጠነ ሰፊ ልዩነት ለመፍጠር በሚችሉበት ሁኔታ ሲገኙ እንኳ ጥበባዊ ችሎታቸውን ያሳዩበታል፡፡ ለዚህም ሁለት ምሳሌዎችን ከታሪክ ልጥቀስ፡፡
  1. ዋሲል ኢብን አጣእ የታዋቂው ኢስላማዊ ምሁር የሐሰን አል-በስሪ ተማሪ ነበር፡፡ ታዲያ ይህ ሰው ከእለታት አንድ ቀን ከአስተማሪው ጋር ክርክር ይገጥማል፡፡ ክርክሩ የተነሳው “አንድ በአላህ የሚያምን ሰው ሀጢአት ቢሰራ ወደ ጀሀነም ይገባል ወይስ አይገባም?” በሚል ጥያቄ ነው፡፡ መምህሩ “ሰውየው ኢማን እያለው ሀጢአት ቢሰራና ተውባ ሳያደርግ ቢሞት ለሰራው ሀጢአት በጀሀነም ይቀጣል፡፡ ነገር ግን ጀሀነም እንደገባ በዚያው አይቀርም፡፡ ቅጣቱን ሲጨርስ ወደ ጀነት ይገባል” በማለት ትክክለኛውን የ”አህሉ ሱንና” መልስ ሰጡት፡፡
ዋሲል ግን “ይህማ አይሆንም፤ ሰውየው በጀሀነምና በጀነት መካከል የሚቆይበት ቦታ መኖር አለበት” በማለት አዲስ ሀሳብ ወለደ፡፡ አስተማሪው “እንዲህ አትበል” ቢሉትም “እንቢ” አለ፡፡ በዚያው ከርሳቸው “ደውር” (የመማሪያ ቦታ) ወጣ፡፡ ይህንን አመለካከት እርሾ በማድረግም “ሙእተዚላ” የተሰኘውን ጥንታዊ ፊርቃ ፈጠረ፡፡ ይህ ፊርቃ በመፈጠሩ ሙስሊሙ ኡማ ለአራት ምእተ አመታት ፍዳውን አየ፡፡ በኋላ ላይ ግን አላህ ፊርቃውን በራሱ ጥበብ አከሰመው፡፡
  1. ታዋቂው ጀግና ኻሊድ ኢብን አል-ወሊድ(ረ.ዐ) ስሙ በጠላቶቹ ፊት እየገነነ በሄደበት ዘመን አንዳንድ ሰሀባዎች ድል የሚያጎናጽፈው አላህ መሆኑን ዘነጉትና “ኻሊድ የሚመራው ጦር ሁሌ አሸናፊ ነው፤ እርሱ ባለበት ቦታ ድል አለ” የሚል አስተሳሰብ አመጡ፡፡ ታዲያ ኸሊፋ ዑመር ኢብን አል-ኸጣብ (ረ.ዐ) ይህንን መጥፎ አመለካከት ለመስበር ፈለጉና ኻሊድን ከቦታው አንስተው አቡ ኡቤይዳ ኢብን ጀራህን (ረ.ዐ) መሾማቸውን የሚገልፅ ደብዳቤ ላኩለት፡፡
   ኻሊድ ደብዳቤው ሲደርሰው በልቡ ቅሬታ ቢገባውም የኸሊፋውን ትእዛዝ ለመፈፀም አላመነታም፡፡ በጊዜው የነበረበት አጣዳፊ ሁኔታ እስኪያልፍለት ድረስ በቦታው ላይ ቆየ፡፡ ከዚያም አዛዥነቱን ያለ አንዳች ክርክር ለአቡ ኡቤይዳ አስረከበና ተራ ወታደር ሆኖ መዋጋት ጀመረ፡፡ ሙስሊሞችም ያለ ኻሊድ መሪነት ድል አደረጉ፡፡ ኻሊድ ሁሉም ነገር ካበቃ በኋላ ወደ ኸሊፋው ዘንድ ሄደና “ምን ጥፋት ሰርቼ ነው የተሻርኩት?” በማለት ጠየቀ፡፡ ኸሊፋውም እውነተኛውን ምክንያት ነገሩት፡፡
   ኻሊድ በዚያን ጊዜ የኸሊፋውን ትእዛዝ አልቀበለም ቢል ምን ይፈጠር ኖሯል? ይህንን የሚያውቀው አላህ ብቻ ነው፡፡ በአለም ታሪክ ከታዩት ክስተቶች ተነስቼ ግምቴን ብሰነዝር ግን ዛሬ የምንማረው የኢስላም ታሪክ በሌላ መልኩ የሚጻፍ ይመስለኛል፡፡ ባጭሩ “አንድ አደገኛ ፊርቃ ተፈጥሮ የሙስሊሙ ዓለም ይከፋፈል ነበር” ያሰኛል፡፡ አላህ እንኳንም አላደረገው! (ደግነቱ ሰውየው ኻሊድ ነው! የአላህ ሰይፍ! እንደ ዋሲል ኢብን አጣ ያለ ተልካሻ ፍጡር አይደለም)፡፡
   ከኻሊድ ታሪክ እንምንረዳው ቅሬታ ሲሰማን የሙስሊሙን ኡማ ለክፍፍል የሚዳርጉ እርምጃዎችን መውሰድ የለብንም፡፡ ቅሬታ፤ ልዩነት፤ አለመግባባት ካለ በጥበብ መያዝና መፍታት ይገባል፡፡
የአህባሽ የስንጠቃ ጥረት እንዳይሰምርለት
   አህባሽ በመሰረቱ “ቀሽም” ፊርቃ ነው፡፡ የእምነት ፍልስፍናውም ሆነ አካሄዱ ጤናማ አእምሮ ያለውን ሙስሊም የመሳብ ሀይል የላቸውም፡፡ አንጃው በሺህ ተከታዮች ብቻ የተገደበው ሀቅን ባለመያዙ ብቻ ሳይሆን ፍልስፍናውን የማስረዳት ብቃትም ስለሌለው ነው፡፡ ዛሬ በሀገር አቀፍ ደረጃ መነጋገሪያ የሆነበት ምክንያት ከጀርባው ያሉ ሐይሎች “እርሱ ይምራችሁ! እርሱ የሚያስተምረውን ፍልስፍና ብቻ ተከተሉ” የሚል አስገዳጅ አካሄድ በመጀመራቸው ነው፡፡
   “አህባሽ” ፍላጎቱ እንደማይሰምርለት እራሱ አበጥሮ ያውቃል፡፡ እስከዛሬ ድረስ ራሱን ከሌሎች ሲያሸሽ የኖረበት ምክንያትም ይኸው ነው፡፡ በዚህ በኩል ስጋት የለብንም፡፡ አህባሽ የኛ ስጋት የሚሆነው ግን እርሱ የሚሰነዝራቸው የማታለያ ዘዴዎች፤ ከልክ በላይ የሚደጋግማቸው የማዘናጊያ አመለካከቶች፤ ሆን ብሎ የሚወረውራቸው የማጭበርበሪያ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ወዘተ.. በኛ ውስጥ ገብተው የልዩነት መስመር ማበጀት ከቻሉ ብቻ ነው፡፡ ባጭሩ አህባሽ በየትም የትም እያለ አንድነታችንን መሰነጣጠቅ ሲችል ፍላጎቱ ሰመረለት ማለት ነው፡፡ ስለዚህ የኡማውን ህብረት የሚንድበት ቀዳዳ እንዳያገኝ በንቃት መጠበቅ ይጠበቅብናል፡፡
   ከታሪክ ምእራፎች እንደምንረዳው ይህ ኡማ አንድነቱን ካጠበቀ ሁሌም ድል ያደርጋል፡፡ አንድነቱን ሲያላላ ግን ጠላቶቹ ይበረክታሉ፡፡ አህባሽም የጠላቶቻችን ፊት አውራሪ ሆኖ ለዘመቻ የመጣው በጠባቂዎቹ ጉልበት ስለተማመነ ብቻ ሳይሆን “አንድነት የላቸውም” የሚል ተስፋ ስለያዘ ነው፡፡
   ስለዚህ ያ ጀመዓ! አህባሽ ወሀቢ የሚለው “አላህ ከአርሽ በላይ ነው” ያለውን ሰው ብቻ አይደለም፡፡ “ካፊር!” በማለት የፈረጃቸው ኡለማ በአንድ መዝሐብ ብቻ የታቀፉ አይደሉም፡፡ ከዚህ ቀደም እንዳስረዳሁት አህባሽ እርሱን የማይቀበሉትን ሙስሊሞች በሙሉ “ወሃቢ ናችሁ“ ነው የሚለው፡፡ የተለያዩ ሰበቦችን እየፈጠረ “ተክፊር” ማወጁም ልማዱ ነው፡፡ ይህ ክፉ ቡድን የደቀነብንን አደጋ በእንጭጩ ለመቅጨት የምንችለው በአንድነት ስንቆም ነው፡፡
   አህባሽና ጀሌዎቹ ትላንት “ኸዋሪጃ” እያሉ ሲዘምሩ አንዳልነበረ ሁሉ ዛሬ “ኸዋሪጃ የለም አክራሪ የተባለ በሙሉ ወሃቢያ ነው“ የሚል መፈክር አምጥተዋል፡፡ ዛሬ “ወሀቢ” የሚለው ቅኝት ነገ ተቀይሮ “ኢኽዋን” የሚል መዝሙር የማይጀመርበት ምክንያት የለም፡፡ ተነገ ወዲያ ደግሞ “ተብሊግ ጠላታችን ነው” ይባል ይሆናል፡፡ ከዚያ በማስከተልም “ሱፊዎች ካፊሮች ናቸው”! ከዚያ በክልልና በብሄረሰብ ላለመምጣታቸው ምንም ዋስትና የለንም፡፡ ዋስትናችን አላህ ብቻ ነው!
ስለዚህ መፈራረጅ፤ መጠላለፍ፤ መሻኮት፤ ወዘተ… ይቅርብን፡፡ ሁሉም የጋራ ህብረት ይፍጠር፡፡ ይህንን የፈተና ጊዜ ህብረታችንን የምናጠናክርበት አጋጣሚ እናድርገው፡፡ እስከዛሬ ላጠፋነውም ተውባ እናድርግ! ሁላችንም ሙስሊሞች ነን!! አላህ በኢስላም ላይ ያጽናን፡፡ ዲናችንን ከጠላቶቹ ይጠብቀው፡፡ የነቢዩን ሱንና በጥበቡ ይጠብቀው፡፡ በነገዋ እለት በርሱ ፊት ከሚዋረዱት አያድርገን፡፡ አንድነታችንን ያጠናክርልን!

No comments:

Post a Comment