Ubah Abdusalam Seid
“የአህባሽ” ጀመዓ ለብዙዎቻችን ስጋት ከሆነባቸው ምክንያቶች መካከል አንዱ የአንጃው አመለካከቱን በህዝቡ ውስጥ ለማስረጽ ሲል ከጸረ-እስላም ሃይሎች ጋር እንኳአንድ ላይ ወግኖ ሙስሊሞችን ከመጉዳት ወደ ኋላ የማይል መሆኑ ነው፡፡ የአንጃውን የኋላ ታሪክ የሚያውቁ ወገኖች ይህንን በስፋት ሲዘረዝሩ ነበር፡፡ ለመሆኑ ይህ ጽንፈኛ አንጃ ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ ሙስሊሞችን እንዲመራ ማን መረጠው?
ይህን ጥያቄ መመለስ ይከብዳል፡፡ ሆኖም አንድ ነገር በእርግጠኛነት መናገር ይቻላል፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት ይህንን ጉዳይ ለብቻው አልወሰነውም፡፡ ነገሩ የበርካቶች እጅ አለበት፡፡ ከሁሉም እጆች የሚተልቀው ደግሞ የአሜሪካ እጅ ይመስለኛል፡፡
አሜሪካ ከመስከረም 11/2011 ወዲህ በሽብር ላይ ጦርነት ከፍቻለሁ ትላለች፡፡ ቀንደኛ አሸባሪዎችን የሚፈለፍለውም “እስላማዊ አክራሪነት ነው” ባይ ነች፡፡ በአሜሪካ አመለካከት “የእስላማዊ አክራሪነት ምንጭ “ወሃቢያ” የሚባለው ቡድን ነው፡ ኢትዮጵያም ወሃቢያ እየተጠናከረ የመጣባት ሀገር ናት፡፡ ስለዚህ የወሃቢያን አክራሪ አቋም ለመቆጣጠር በርካታ ዘዴዎችን መጠቀም ያፈልጋል፡፡ ከነዚህም ውስጥ አንዱ ከሙስሊሞች መካከል ከወሀቢያ ጋር ፈጽሞ የተቃረነ ትምህርትና የእምነት ፍልስፍና ያላቸውን ግለሰቦችና ቡድኖች ማጠናከርና በወሃቢያ ላይ የበላይ እንዲሆኑ መርዳት ነው፡፡” በዚህ ስሌት መሰረት ነው እንግዲህ “አህባሽ” በአለም አቀፍ ደረጃ የተመረጠልን፡፡ ለመሆኑ ይህንን ጥቆማ ለአሜሪካ የሰጠው ማን ነው?
ብዙዎች አህባሽን “ለኢትዮጵያ የመረጡት ፕሮፌሰር ሀጋይ ኤርሊች ናቸው” ይላሉ፡፡ እኔ ግን ሀጋይ ኤርሊችን ብቻ አልጠረጥርም፡፡ ከሀጋይ ኤርሊች በላይ በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር የነበሩትን ዴቪድ ሺንን እጥረጥራለሁ፡፡ ምክንያቱም ሃጋይ ኤርሊች ነገሩን በይፋ በማቀንቀን የመጀመሪያ ሰው ይሁኑ እንጂ አህባሽ በኢትዮጵ ውስጥ ቢናጠከር ለኢትዮጵያም ሆነ ለአሜሪካ ጥቅም የሚበጅ እንደሆነ በፖሊሲ ደረጃ ሲሰብኩ የነበሩት ዲቪድ ሺን ነበሩ፡፡ ለዚህም አምባሳደር ዴቪድ ሺን በዲሴምበር 20/2004 ቤይሩት በሚገኘው የአሜሪካ ዩኒቨርሲቲ (American University of Beirut) “እስልምናና ግጭቶች በአፍሪካ ቀንድ?” በሚል ርዕስ ያቀረቡት ጥናታዊ ጽሁፍ ግንባር ቀደም ሆኖ ይጠቀሳል፡፡ (የዴቪድ ሺንን ጽሁፍ ከሚቀጥለው ዌብሳይት ማግኘት ትችላላችሁ፡፡ ጽሁፉ ሰፊ ስለሆነ ከቻላችሁ ሁሉንም አንብቡት፡፡ ካልቻላችሁ እኛን የሚመለከተውን ክፍል ብቻ አንብቡ፡፡ http://www.ephrem.org/dehai_archive/2005/nov04-jan05/0562.html )
ዲቪድ ሺን ከዚያ በፊትም ሆነ በኋላ በአፍሪካ ቀንድ ጉዳዮች ላይ በርካታ የፖሊሲ ጥናቶችን አቅርበዋል፡፡ ይህ ጽሁፋቸው ግን “አህባሽ በአሜሪካ መንገድ ላይ ይለፍ” የሚለውን አረንጓዴ መብራት ያበራ እንደሆነ ከአቀራረቡ መረዳት ይቻላል፡፡
ዲቪድ ሺን ከሰባት ዓመት በፊት የተነፈሱት የፖሊሲ ሀሳብ በሙከራ ደረጃ በስራ ላይ ሲውል ቆይቷል፡፡ ለዚህም አንዳንድ መረጃዎችን ልስጣችሁ፡፡
- የአሜሪካ ኤምባሲ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ሲያዘጋጃቸው የነበሩት የረመዳን የኢፍጣር ፕሮግራሞች (በዚህ ፕሮግራም ላይ እንዲገኙ ሲጋበዙ የነበሩት እነማን ናቸው? እንዴትስ ነው የሚመረጡት? )
- አሜሪካ በራሷ በጀት በባሌ የሚገኘውን የዲሬ ሼኽ ሁሴን መስጊድና የመቃብር ቦታ ማሰደሷ(አሜሪካ “ወሃቢዎች ዲሬ ሼኽ ሁሴን የመሳሰሉትን ቀደምት መስጊዶችና የመቃብር ቦታዎች ማጥፋት ይፈልጋሉ፡፡ ስለዚህ ሱፊዎች የሚጎበኟቸውን የመቃብር ቦታዎችና ሀድራዎች ማጠናከር ያስፈልጋል” ትላለች፡፡)
- ባለፉት ሁለት ዓመታት በተካሄዱት የመጅሊስ ምርጫዎች “ወሀቢዎች” እስከ ወረዳ ድረስ ባለው ባሉት ኮሚቴዎች እንዳይሳተፉ በሚል ሰበብ ሲሰሩ የነበት የምርጫ ቲያትሮች
ነገሩ ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶት በትጋት ሲካሄድ ነበር፡፡ ይህንንም አምባሳደር ዶናልድ ያማሞቶ በጻፉትና ዊኪሊክስ በኢንተርኔት በለቀቀው የቴሌግራም ዘገባ በስፋት ነግረውናል፡፡ (ቴሌግራሙን ለማንበብ የሚቀጥለውን የዊኪሊክስ ገጽ ይክፈቱ http://wikileaks.org/cable/2009/07/09ADDISABABA1674.html )
የሚገርመው ነገር የትኛውም የአህባሽ ጀመዓ አባል ይህንን ጉዳይ የማያስተባብል መሆኑ ነው፡፡ እንደ አህባሾች አመለካከት “ወሀቢያ የተባለው ቡድን እስልምናን ለማጥፋት በሙሉ ሃይሉ የሚሰራ የሙናፊቆች ስብስብ ነው፡፡ ስለዚህ እርሱን በተቻለው መንገድ ሁሉ መታገል ያስፈልጋል፡፡” አህባሾች በቀጥታ የሚሉት ይህንን ነው፡፡
ታዲያ ምን ይዋጠን! “አህባሽ” ስለማንቀበለው ብቻ በተለመደው ጽንፈኛነቱ “ወሃቢያ ናችሁ!” ይለናል፡፡ አሁንማ “ባለቤቷን የተማመነች በግ ላቷን ውጪ ታሳድራለች” አይነት ነገር ሆኖብናል፡፡ አሜሪካን ተጠግቶ እኛን ሊፈራ?አላህን ያልፈራ እኛን እንዴት ይፈራል!
ስለዚህ ከሰሞኑ ስጋታችን በጣም ጨምሯል፡፡ በአሜሪካ አጋፋሪነት ስለ “ወሃቢያ” እና ስለ “ሱፊያ” በጥልቀት የማያውቀውን የኢትዮጵያ መንግስት አሳስቶ ጉድ እንዳይሰራን ብቻ!! ከሰሞኑ ግር ግር እንደማየውማ “ወሃቢያ ናችሁ” በሚል የጸረ-አሸባሪነት ህግ የሚባለውን አሳሳቢ አዋጅ በሙስሊሞች ላይ እያስመዘዘ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ለስቃይ እና ለእንግልት እንዳይዳርግ ያሰጋናል፡፡ ስለዚህ ስጋታችን “ስጋት” ብቻ ሆኖ እንዲቀር ትግላችንን በዚህ አቅጣጫ መቀየስ የሚገባ ይመስለኝ፡፡
ያ ጀመዓ! እኔ ይህንን ብያለሁ፡፡ እናንተስ ምን ትላላችሁ? አህባሽ “አህሉ ሱንና ወልጀመዓ” የሚለውን ስም በውሸት ደርቦ “ወሃቢ ናችሁ” እያለ የፈለገውን ሊፈጽምና ሊያስፈጽም አሰፍስፏል፡፡እርሱን በመመከቱ ዙሪያ በጋራ እንወያይ፡፡ ሀቅን እስከያዝን ድረስ የአላህ እርዳታ ከኛ ጋር ነው፡፡
በሉ ሀሳብ ስጡ ያ ጀመዓ!!
ወሰላሙ ዓሌይኩም ወራህመቱላህ!!
No comments:
Post a Comment