Tuesday, October 18, 2011

“አህባሽ” ሆይ! የሱስንዮስና የአጼ ዮሀንስ ዘመን አልፏል!


Ubah Abdusalam
የኢትዮጵያ ታሪክ በጦርነትና በፍትጊያ የተሞላ ነው፡፡ ከነዚህ ጦርነቶች መካከል አብዛኛዎቹ በእብሪተኛ መሪዎች ቀስቃሽነት ነበር የተካሄዱት፡፡ ዓለም በስልጣኔና ጎዳና ወደ ፊት ሲገሰግስ የያኔዎቹ የኢትዮጵያ መሪዎች ግን “እኔ አውቅልሀለሁ” በሚል ጀብደኝነታቸው ህዝቡን እርስ በራሱ ያጫርሱት ነበር፡፡ አንዳንድ መሪዎችማ ህዝቡ የቀድሞ እምነቱን ትቶ እነርሱ የመረጡለትን ጎዳና እንዲከተል ለማስገደድ ሲሉ ህዝቡን ከፍተኛ እልቂት ባስከተሉ ጦርነቶች ውስጥ ሲዘፍቁት ኖረዋል፡፡ ነገር ግን እነርሱ የፈለጉት ሃይማኖትን የማስቀየር ፖሊሲ አልተሳካላቸውም፡፡ ይህንንም በሁለት ምሳሌዎች መግለጽ ይቻላል፡፡ 
  •   አጼ ሱስንዮስ (ከ1605-1632)፡- አጼ ሱስንዮስ ከምዕራብ አውሮፓ (ፖርቱጋልና እስፔን) በመጡት የካቶሊክ እምነት ሰባኪያን ተማርኮ ሃይማኖቱን ለወጠ፡፡ ሳይውል ሳያድርም በሀገሪቱ ውስጥ ያሉት ካህናት፤ ቀሳውስትና መላው የክርስቲያን ህዝብ የኦርቶዶክስ ሃይማኖቱን ትቶ ወደ ካቶሊክ እምነት እንዲገባ አዋጅ አስነገረ፡፡ ህዝቡ ግን ትዕዛዙን “አልቀበልም!” አለ፡፡ በነገሩ የተናደደው አጼም ፍላጎቱን በሃይል ለመፈጸም ተነሳ፡፡ መላው ሰራዊቱን በክርስቲያኑ ህዝብ ላይ አዘመተ፡፡ ህዝቡም ከሱስንዮስ ሰራዊት ጋር ተጋፈጠ፡፡ በሀገሪቱ ላይ የጦርነት እሳት ነደደ፡፡
  አጼ ሱስንዮስ ጀብደኝነት ባሳወረው ወኔው በጦርነቱ ገፋበት፡፡ ለ27 አመታት በዘለቀው የስልጣን ዘመኑ ምንም ሳይሰራበት ሀገሪቷን በጦርነት እሳት ሲለበልባት ቆየ፡፡ እርሱ የለኮሰው እሳት የቆመው አጼው “አለም በቃኝ” ብሎ ወደ ገዳም ሲገባና ልጁ ፋሲል በአባቱ ቦታ ንጉስ ተብሎ ሲሾም ነው፡፡
(ይህ ምሳሌ የሚመለከተው ክርስቲያኖችን ነው፡፡ ቢሆንም ክርስቲያን ወገኖቻችን አሁን እኛን የገጠመን ፈተና በሱስንዮስ ዘመን ያጋጠማቸውን ፈተና ያህል ከባድ እንደሆነ እንዲረዱልን ስለምፈልግ በምሳሌነት ጠቅሼዋለሁ)፡፡ 
  • አጼ ዮሀንስ አራተኛ (ከ1870-1888)፡ አጼ ዮሀንስ “በአንድ ሀገር አንድ ሃይማኖት” በሚለው ፖሊሲያቸው ይታወቃሉ፡፡ ይህንን ፖሊሲ በስራ ላይ ለማዋል ሲሉ ከታናሻቸው ከምኒልክ ጋር እንኳ ተጣልተዋል (ምኒልክ ጥሩ ባይባሉም በሃይማኖት ፖሊሲያቸው ከዮሀንስ ይሻላሉ)፡፡
አጼ ዮሀንስ ፖሊሲያቸውን ለመተግበር ሲነሱ በቅድሚያ የመረጡት የወሎ ክፍለ ሀገርን ነው፡፡ በዚሁ መሰረትም ለብዙ ምዕተ አመታት እምነታቸውን አስጠብቀው የቆዩት የወሎ ሙስሊሞች በአንድ ወር ውስጥ ክርስትና ካልተነሱ በሰይፍ እንደሚቀጡ አዋጅ ተነገረ፡፡
ወላዋዩና ሹመት ፈላጊው (እንደ ራስ ሚካኤል አይነቱ) የአጼውን ትእዛዝ ለመፈጸም ተሸቀዳደመ፡፡ አብዛኛው ህዝብ ግን እስልምናን በምንም ዋጋ እንደማይለውጥ ለአጼው ቁርጡን ነገራቸው፡፡ በነገሩ የተናደዱት አጼ ዮሀንስ የሽብርና የጦርነት ጅራፋቸውን በወሎ ህዝብ ላይ መዘዙ፡፡ ሙስሊሙ ህዝብ በሼኽ ጠለሃ ጃዕፈር፤ በአብደላ ጪፍራ፤ በአባ ዋጠው እና በሌሎችም ሙጃሂዶች ዙሪያ በመሰለፍ እብሪተኛውን አጼ ተጋፈጠ፡፡ የአጼው ጥቃት እየባሰበት ሲሄድም ሙስሊሙ ህዝብ ለሃይማኖቱ ሲል ወደ ሀረር፤ ባሌ፤ ጅማ እና ጉራጌ ተሰደደ፡፡ ነገሩ አንጀቱን ያሳረረው ደግሞ ወደ ሱዳን እተሰደደ ከኢማም አህመድ አልማህዲ ጦር ጋር ተቀላቀለ፡፡
አጼው በጦርነት ፖሊሲያቸው ገፉበት፡፡ ሆኖም ጦርነቱ ሃይማኖትን ሊያስለውጥ አልቻልም፡፡ እንዲያውም የርሳቸው ህይወት እንዲቀጠፍ ምክንያት ሆነ፡፡
ከላይ የጠቀስናቸው ሁለት ምሳሌዎች በርካታ ቁምነገሮችን ያስተምሩናል፡፡ ምሳሌዎቹን በትክክለኛ አእምሮ ያነበበ ሰው በኢትዮጵያ ውስጥ እምነትን በግድ ለመጫን የሚደረግ ጥረት መጨረሻው ውድቀት እንደሆነ በደንብ ይገነዘባል፡፡
ዛሬ አለም በሰለጠነበትና ጭፍንነትና አጉል አክራሪነት አንድ እርምጃ እንኳበማያራምዱበት ዘመን አህባሾች “አይናችሁን ጨፍኑ ላሞኛችሁ” ሊሉን መጥተዋል፡፡ ከኋላቸው በሚገፋቸው ስውር እጅ (አሜሪካ) እየታገዙ የመጅሊስን ስልጣን በመቆጣጠራቸው ብቻ ድል የሚቀናቸው እየመሰላቸው ነው፡፡ ህዝቡ ግን “እስከዛሬ የተከለተላችሁት እምነት ስህተት ስለሆነ በአዲስ መልክ ወደ እስልምና ግቡ” ሊሉት የመጡ መሆናቸውን በደንብ ያውቃል፡፡ የዓለም ህዝብ የሚያምንባቸውንና ለሃይማኖታቸው ከልባቸው ሲሰሩ የቆዩትን ኡለማ “ካፊር ናቸው” እያሉ በመሳደባቸው ብቻ ልቡ ቆስሏል፡፡
ስለዚህ አህባሾች የመጅሊስን ስልጣን ቀርቶ የሀገሪቱን ስልጣን ሙሉ በሙሉ ቢቆጣጠሩ እንኳ የሚለውጡት አማኝ ያለ አይመስለኝም፡፡ ይህ ህዝብ አያቶቹ ከነ አጼ ዮሐንስ ጋር እየተጋፈጡ የጠበቁትን እስልምና በተራ ጮሌነት ያስረክባል ብለው ገምተው ከሆነ በህልም አለም ውስጥ ነው ያሉትና ህዝቡ ራሱ “ከህልማችሁ ንቁ!”ይላቸዋል፡፡ እውነታው ደግሞ በተግባር ይታያል፡፡
ድል የኢስላም ነው!! አላሁ አክበር!!

No comments:

Post a Comment