Tuesday, February 7, 2012 at 11:23pm ·
አህባሾች ስንት ዓይነት እንደሆኑ አውቃችኋል? መለያ ባሀሪዎቻቸውንስ? ይህ ጽሁፍ በነዚህ ጉዳዮች ላይ ያተኩራል። ከዚያ በፊት ግን
- በጽሁፉ የተጠቀሱት በሀገራችን ውስጥ ተሰራጭተው የምናገኛቸው የአህባሽ ሰዎች ብቻ መሆናቸውን ለማሳወቅ እፈልጋለሁ፡፡
- አሕባሽ ሲባል በእንግሊዝኛ ስሙ Association of Islamic Charitable Projects የሚባለውንና በአዲስ አበባ ከተማ ጦር ሀይሎች አካባቢ የማስተማሪያና የሰበካ ማዕከል (መርከዝ) ያለውን ድርጅት ብቻ እንደሚጠቁም መታወቅ አለበት። አንዳንድ ሰዎች መውሊድ የሚያከብረውን የህብረተሰብ ክፍል ወይም በተለምዶ “ሱፊ” ነኝ የሚሉትን ሙስሊሞች በጅምላ እንደ “አሕባሽ” አድርገው የሚፈርጁበት አካሄድ ሙሉ በሙሉ የተሳሳተ ነው። እኛ ጥላችን ቀደም ብዬ በገልጽኩት ድርጅት ስር ታቅፈው የተበከለ አቂዳ እያስተማሩ “ከኛ በስተቀር ሌላው በሙሉ ካፊር ነው፣” ከሚሉትና ለሙስሊሞች መልካም ተግባር የፈጸሙ ዑለማዎቻችን ላይ “የወሃቢያ አባት” እያሉ የተክፊር ፈትዋ ከሚያውጁት ጽንፈኛ የአይሁድ ወዳጆች ጋር ብቻ ነው። (አሕባሽ ማለት በሚከተለው ዌብሳይት የተመዘገበው ድርጅት ነው www.aicp.org)
በዚህ ወቅት በሀገራችን ውስጥ የተበተኑትን አህባሾች በአራት ቡድኖች ከፍሎ ማየት ይቻላል፡፡
ሀ/. ዓለም አቀፍ አህባሾች ፡- እነዚህኛዎቹ አህባሾች በሀገራችን ውስጥ በብዛት የሉም፡፡ ሆኖም በመርከዞቻቸው በአስተማሪነት የሚመደቡት እነርሱ ናቸው፡፡ ከነርሱ ውስጥም የሚበዙት የሊባኖስ አረቦች ናቸው ፡፡ ከተማሪዎቻቸውና ከሌላው ህዝብ ጋር የሚነጋገሩትም በአረብኛ ነው (በሌላ ቋንቋ ሲነጋገሩ አይቼ አላውቅም)፡፡ ከዋናው ሼኽ አጠገብ ደግሞ ሁለት ያህል ረዳት ኡስታዞች ይመደባሉ፡፡ እነዚህኛዎቹ ኡስታዞች ኢትዮጵያዊያንም ሊሆኑ ይችላሉ)፡፡
እነዚህ ሊባኖሳዊ አህባሾች ለ”ወሀቢያ” ያላቸው ጥላቻ የትየለሌ ነው፡፡ በምሳ ሰዐትም ሆነ በትምህርት ክፍለ ጊዜ የሚያወሩት ስለ “ወሃቢያ” ነው፡፡ ኢብን ተይሚያህን ሳያወግዙ ቀኑ አይመሽላቸውም፡፡ ታዲያ ሊባኖሳዊያኑ ውሸትን ተክነውበታል፡፡ ደኢፍ የሆነውን ሀዲስ ሰሒህ፤ ሰሒህ የሆነውን ሀዲስ ደኢፍ አድርጎ ማውራት ለነርሱ ቀላል ነው፡፡ ነገር ግን እነርሱን ሆን ብሎ የተከታተላቸው ሰው ቀጣፊነታቸውን በጥቂት ቀናት ውስጥ ለማወቅ ይችላል፡፡
ለ/. የሀገር ውስጥ ጽንፈኛ አህባሾች፡- ከኢትዮጵያዊያን አህባሾች መካከል አንዳንዶቹ የለየለት ጽንፈኝነት ይታይባቸዋል፡፡ እነዚህ ወገኖች ከነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ) በላይ የአህባሽን መስራች ነው የሚያደንቁት፡፡ ለትንሽ ለትልቁም “ሼኽ እንዲህ ብለዋል” ማለት ይቀናቸዋል፡፡ ከነርሱ ጋር ያልተሳሰረውን ሁሉ “ካፊር ነው” ብሎ የመጥራት አባዜ ተጠናውቷቸዋል፡፡ ይህንንም የምትረዱት ከነርሱ ጋር ክርክር ስትጀምሩ ነው፡፡ ለምሳሌ በኢብን ተይሚያህ ዙሪያ ክርክር ጀምራችሁ “እርሱ እኮ ትክክለኛ ሙስሊም ነው” ካላችሁ በቀጥታ ነው የሚያከፍሯችሁ፡፡
እነዚህ ጽንፈኛ አህባሾች ከሌላው የማህበረሰብ ክፍል ጋር ብዙም አይቀላቀሉም፡፡ ከስራ ሰዓት ውጪ ያለውን ጊዜ የሚያሳልፉት በመርከዝ፤ በቤት ወይም እንደነርሱ የአህባሽ ተከታይ በሆነ ግለሰብ ቤት ነው፡፡ በሌላ በኩል ጽንፈኞቹ አህባሾች ከሌሎች ሰዎች ጋር በጀመዓ አይሰግዱም (ሰውየው አህባሽ ካልሆነ በስተቀር)፡፡ የጁምዓ ሰላትን በየትኛውም መስጊድ አይሰግዱም፡፡ ምክንያታቸውን ስትጠይቁ “ኢማሙ የአቂዳ ችግር አለበት” ይላሉ፡፡ ከጥቂት ጊዜ ወዲህ የራሳቸውን ጁምኣ እየመሰረቱ እንደሆነም ሰምተናል፡፡
ከጽንፈኞቹ አህባሾች መካከል አንዳንዶቹ ኮፍያና ጀለቢያ ማድረግን ይወዳሉ፡፡ ሴቶቹ ግን ሙሉ አባያ ይለብሱና ከስር የጂንስ ሱሪ ያደርጋሉ፡፡ ሴቶቹ በቡድን ተሰብስበው ወደ መርከዝ ሲሄዱ ያያቸው ሰው ይህንን በደንብ ይረዳል፡፡ ሆኖም ጽንፈኞቹ ታይት ሱሪ አያደርጉም፡፡ አንዳንድ ሰዎች “አህባሽ” ስለሆኑ ብቻ “ሴቶቻቸው ታይት እየለበሱ መርከዝ ይገባሉ” እያሉ በሀሰት ይወነጅሏቸዋል፡፡ ይህ ግን ትክክል አይደለም፡፡ታይት ወይም ጅንስ እየለበሱ ጸጉራቸውን ብቻ የሚሸፍኑት ለዘብተኞቹ ናቸው (ከወደ ታች እንመጣበታለን)፡፡
ታዲያ እንደ ሊባኖሳዊያኑ ሁሉ ጽንፈኞቹ አህባሾችም ወሬያቸው “ወሀቢ.. ወሀቢ..ወሀቢ..” የሚል ቅኝት ያለው በመሆኑ ከአንድ ቀን በላይ አብራችሁ መቆየት አትችሉም፡፡ በቶሎ የምትናደዱ ከሆነ ከነርሱ ጋር ባትቀራረቡ ይሻላል፡፡
እነዚህን ጽንፈኞች ወደ ትክክለኛው መንገድ መመለስ ቀርቶ በትእግስት ማዳመጡ ራሱ በእጅጉ ይከብዳል፡፡ ስለዚህ ዳኢዎች በነርሱ ላይ ጊዜ ባያጠፉ ይመረጣል፡፡ ሆኖም እነርሱን መለየቱ በጣም ቀላል እንደሆነ መታወቅ አለበት፡፡ ለምሳሌ ከላይ ያነሳሁትን “ወደ ጀመዓ እና ጁምአ አይመጡም” የሚለውን አባባል የተከተለ ሰው ጽንፈኞቹን በቀላሉ ለመለየት ይችላል፡፡
ሐ/. የሀገር ውስጥ ለዘብተኛ አህባሾች፡- ከአህባሾቹ መካከል ከማንኛውም ሰው ጋር የሚቀራረቡ ለዘብተኞችም አሉ፡፡ እነዚህ ወገኖች ሰላተል ጀመኣንም ሆነ ጁምአን ከኛ ጋር ሊሰግዱ ይችላሉ፡፡ ከስራ ሰኣት ውጪም ከኛ ጋር ሊቀላቀሉ ይችላሉ፡፡ እነዚህኛዎቹም ቢሆኑ ግን የአህባሽ መለያዎቻቸውን አይተውትም፡፡ “ወሀቢ” ማለቱን፤ ኢብን ተይሚያህን መዝለፉን፤”ገውሠል አዘም መጀመን” ማለቱን ወዘተ.. አይተውትም፡፡ በነርሱ ላይ የሚታየው ጥሩ ነገር እንደ ጽንፈኞቹ “ከፈርክ” የሚል ቃል የማይወጣቸው መሆኑ ነው፡፡ በተጨማሪም “ወሀቢ”ን በየደቂቃው እየደጋገሙ ጭንቅላታችሁን አያሳሙምትም፡፡ ከእንዲህ አይነቱ አህባሽ ጋር በዲን ጉዳይ ጨዋታ ጀምራችሁ አካሄዱ ሳይጥማችሁ ቢቀርና “ወሬ ቀይር” ብትሉት እንደ ጽንፈኞቹ አያኮርፍም፡፡
በሌላ በኩል ለዘብተኛ የአህባሽ ሴቶች በጣም ዘናጮች ናቸው፡፡ ከወጣቶቹ መካከል ከፊሉ አባያ ይለብሳሉ፡፡ ብዙዎቹ ግን ጅንስ ሱሪ ነው የሚለብሱት፡፡ የተወሰኑት ደግሞ ወደ ታይት ሱሪ ያደላሉ፡፡ በእድሜ የገፉት “ዲሪአ” ወይም “አባያ” ይብሳሉ፡፡
ታዲያ አንድ ሀቅ መረሳት የለበትም፡፡ እነዚህን ለዘብተኛ አህባሾች ወደ አህባሽ ጀመኣ ያስጠጋቸው የእውቀት ማነስ ነው፡፡ ከፊሎቹ ደግሞ በጓደኞችና በዘመዶቻቸው ግፊት ነው ወደ አህባሽ የሚሄዱት፡፡ ትእግስት ያለው ሰው ጊዜ ወስዶ ዳእዋ ካደረገላቸው ወደ ትክክለኛው መንገድ ሊመለሱ ይችላሉ፡፡
መ/ “አኩራፊ አህባሾች”፡- እነዚህኛዎቹ አህባሾች በትልልቅ ከተሞች አካባቢ የሉም፡፡ ብዙዎቹ በአነስተኛ ከተሞችና በአንዳንድ የገጠር ክፍሎች ይገኛሉ፡፡ ከነርሱ መካከል አብዛኛው ስለሼኽ አብዱላህ አል-ሐረሪም ሆነ ስለ አህባሽ ምንም ሳያውቅ በንዴት ብቻ ከአህባሾች ጋር ግንኙነት የመሰረተ ነው፡፡ እነዚህ ወገኖች የት ነው ያሉት? ይህንን ማስረዳት ቀላል ነው፡፡
በሀገራችን ውስጥ ሰዎች ለዚያራ የሚጎርፉባቸው የአውሊያ ደሪሆችና ሀድራዎች በብዛት አሉ፡፡ ለምሳሌ የባሌው ዲሬ ሼኽ ሁሴን፤ የወሎው ጀማ ንጉስ፤ አኒይ፤ ዳኒይ፤ ወዘተ.. የጉራጌዉ የቃጥባሬ ሀድራ፤ በምስራቅ ኢትዮጵያ ልዩ ልዩ ቦታዎች ያሉ ሀድራዎች ወዘተ… ይጠቀሳሉ፡፡ የነዚህ ደሪሆችና የሀድራ አስተዳዳሪዎች የሚከተሉት እስልምና ከትክክለኛው እስልምና በእጅጉ ይራራቃል፡፡ ባህልና ልማድ ተቀላቅለውበታል፡፡
ባለፉት ሀያ አመታት ውስጥ ዳኢዎች ሰለ “አላህ” ተውሂድ ሲያስተምሩ እነዚህ የሀድራ ሰዎች “ከአባቶቻችን የወረስነውን ዲን ለማራከስ ነው የመጣችሁት” በማለት ከዳኢዎች ጋር ግብግብ ይገጥሙ ነበር፡፡ “ወሀቢ” እያሉ ይወርፏቸዋል፡፡ እንደዚያም ሆኖ ግን “ወሀቢ” ከሚሉት ቡድን ጋር አልተቆራረጡም፡፡ ሁለቱም በአንድ መስጊድ በሚሰገድ የተራዊህ ሰላት ላይ በሀይለኛ ሁኔታ ተጣልተው በማግስቱ አንድ ላይ የሚሰግዱበት ሁኔታ አለ፡፡ የዚህ ምክንያቱ ሁለቱም “ከፍረሃል” የማይባባሉ በመሆናቸው ይመስለኛል፡፡
ነገር ግን ወጣቱ ክፍል የተውሂድን ትርጉም እየተረዳ በመምጣቱ ከዚያራና ከሀድራ እየሸሸ ነው፡፡ በዚህም የተነሳ የሀድራ ሰዎች “ወሀቢያ” በሚሉት የወጣቱ ክፍል ላይ የቋጠሩት ቂም እንዳለ ነው ያለው፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ “አህባሽ” እነዚህን “አኩራፊ” ወገኖቻችንን እያደነ “እጅግ የረቀቀ” ፍልስፍናውን እያስተማራቸው ነው፡፡ በዚህም የተነሳ ጥንት በሀድራ ሰዎች ዘንድ የማይታወቀው “ኢብን ተይሚያህ” ዝነኛ ሰው እየሆነ ነው፡፡ (ማለትም የሀድራ ሰዎች “ወሀቢ” የሚባለው ቡድን የሼይኽ ሙሀመድ ኢብን አብዱል ወሃብን ትምህርት የሚከተል እንደሆነ ነው የሰሙት፡፡ አህባሽ ግን “ወሀቢ”ን የጀመረው ኢብን ተይሚያህ የሚባል ፈላስፋ ነው” እያለ ያስተምራቸዋል፡፡)
እነዚህ ወገኖች የአህባሾች ሰለባ የሚሆኑት ዳኢዎች በሚያሳዩዋቸው የሂክማ (አካሄድና አቀራረብ) ጉድለቶች ነው፡፡ ለምሳሌ አንዳንድ ዳኢዎች “ሀቅ መደበቅ የለበትም” ይሉና ሰውየው እንዲገለጽበት የማይፈልገውን ደካማ ጎኑን ይነካኩታል፡፡ አንዳንዶቹ ዳኢዎች ጭራሽ ከመስመር ይወጣሉ፡፡ (ለምሳሌ የሽርክን አስፈሪነት በዘዴ እየተነተነ ማስተማር የነበረበት አንድ ዳኢ የአንድ ታዋቂ ቤተሰብን ስም እየጠቀሰ “እነ እገሌ እኮ ሙሽሪኮች ናቸው” እያለ ዳእዋ ሲያደርግ አጋጥሞኛል)፡፡ በዚህም የተነሳ የሀድራ ሰዎችና በሀድራ ዙሪያ የሚኖሩ ማህበረሰቦች በእልህ ወደ አህባሽ ይከበልላሉ፡፡
ስለዚህ እነኝህ ወገኖቻችን የአህባሽ ሰለባ እንዳይሆኑብን ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ዳኢዎች የአላህን ቃል በሂክማና በጥበብ ማስተማር አለባቸው፡፡
አህባሾች በኔ ትንተና ይህንን ይመስላሉ፡፡ ከኔ በበለጠ ሁኔታ ስለ አህባሽ የሚያውቁ አንባቢዎች የሚያዉቁትን ሁሉ ለወንድሞቻችንና ለእህቶቻችን እንዲናገሩ በአክብሮት እጠይቃለሁ፡፡ አላህ ከአህባሽና ከፈተናው ይጠብቀን፡፡
ድል የኢስላም ነው፡፡ አላሁ አክበር!!!!
No comments:
Post a Comment