Friday, May 11, 2012

የአሕባሽ የሰበካ ስልቶችና የጥቃት ዒላማዎች

Ubah Abdusalam Seid 

Thursday, February 9, 2012 at 11:49pm


 
አህባሾች ምን አይነት ሰዎችን ነው ለጀመኣ አባልነት የሚመለምሉት? ምን አይነት ስልቶችን ነው የሚጠቀሙት? በዚህ ጽሁፍ  በነዚህ ላይ እናተኩራለን፡፡
በሀገራችን ያለው የአህባሽ ጀመዓ ስርጭት
  ዛሬ አህባሽ ጠንካራ ጀመኣ የመሰረተባቸው ከተሞች
  • አዲስ አበባ (ትልቅ መርከዝ አለው)
  • ሀረር (መርከዝ አለው)
  • ድሬዳዋ (መርከዝ ያለው አልመሰለኝም)
  • ጎንደር (ጀመኣው ጠንካራ ነው ይባላል፡፡ ሆኖም የራሳቸው መርከዝ ያላቸው መሆኑን አላረጋገጥኩም)፡፡
   የ“አህባሽ”ን ፍልስፍና በትክክል የሚያውቁ ሰዎች ያሉት በነዚህ ከተሞችና በአካባቢያቸው ነው፡፡ ከነርሱ ውስጥም ብዙዎቹ ወደ መርከዝ እየሄዱ የታእሊም ፕሮግራማቸውን ይከታተላሉ፡፡ አንዳንዶቹም (በተለይም የቢሮ ሰራተኛ የሆኑት) እሁድና ቅዳሜ ወደ መርከዝ ይሄዳሉ፡፡
  አህባሽ መሰረቱን ለማስፋት ጥረት የሚያደርግባቸው ሌሎች ቦታዎች
  • በኦሮሚያ ክልል ብዙ ስፋራዎች
  • በወሎ ክፍል ሀገር በብዙ ስፍራዎች
  • በትግራይ ክልል አንዳንድ ስፍራዎች ናቸው፡፡
   በነዚህ አካባቢዎች “ወሀቢያ የአባቶቻችንን እምነት አራክሷል” በማለት ያኮረፉ በርካታ ሰዎች በመኖራቸው ነው አህባሽ በነርሱ ላይ ትኩረት ያደረገው፡፡ አንጃው ከነርሱ ጋር ግንኙነት መፍጠር የጀመረው ቆይቶ ነው፡፡ ምክንያቱም በሀገራችን ውስጥ የተከለው ማዕከል ውሱን አቅም ነው ያለው፡፡ በሌላም በኩል አህባሽ “ትክክለኛው የአህሉ-ሱንና አቂዳ እኔ ጋር ነው ያለው” በማለት ስለሚጀነን (ስለሚኩራራ) እነዚህን አኩራፊ ወገኖች  ዝቅ አድርጎ የማየት ነገርም አለበት፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ከአኩራፊዎቹ ጋር ያለውን ቀረቤታ እያሻሻለ ነው፡፡ ለምሳሌ የአህባሽ ቀንደኛ ሰዎች ከአኩራፊዎቹ ጋር መቀራረብ፤ በነርሱ ጀመዓ መስገድ ወዘተ… የመሳሰሉ ለውጦችን እያሳዩ ነው ፡፡
   አኩራፊዎቹ እስካሁን ድረስ የአህባሽን ፍልስፍና ሙሉ በሙሉ የተረዱት አይመስለኝም፡፡ ለምሳሌ “አላሁማ አጂርና ሚነን-ናር” (አላህ ሆይ! ከእሳት ቅጣት ጠብቀን) የሚለው ታዋቂ ዱኣ በአህባሽ ዘንድ እንደማይፈቀድ አኩራፊዎቹ የሰሙት አይመስለኝም፡፡(ይህ ዱኣ በወሎ ገጠራማ መንደሮች ባሉ ሀድራዎች የሚማሩ ደረሳዎች በጀመዓ የሚያደርጉት ታዋቂ ዱዓ ነው)፡፡
የአህባሽ ዒላማዎች
   አህባሽ በጣም የሚያተኩረው ለአቅመ አዳም ባልደረሱ ልጆች ላይ ነው፡፡ በተለይ ቁርአንና አረብኛን በቤትና በመድረሳ አካባቢ የተማሩ ህጻናትን ወደ ጀመኣው ለመቀላቀል ከፍተኛ ጥረት ያደርጋል፡፡ አንጃው ይህንን የሚያደርግበት ምክንያት ግልጽ ይመስለኛል፡፡ መናገር ካስፈለገም እነዚህ ህጻናት ሌላ አይነት የአቂዳና የፊቅህ ትምህርት ስላልተማሩ የአንጃውን ፍልስፍና ያለአንዳች ክርክር ይቀበሉለታል፡፡ ከትምህርት በኋላም አንጃው በሚፈልገው መልኩ እነርሱን ማሰማራቱ ችግር አይሆንበትም፡፡
   ከአዋቂዎች መካከል አንጃው የሚያተኩረው
  • ከላይ የጠቀስኳቸው አኩራፊዎች በሚበዙባቸው አካባቢዎች ያሉ ማህበረሰቦች (ለምሳሌ የባሌው ሼኽ ሁሴን መካነ መቃብር ባለበት ስፍራ የሚኖሩ ሰዎች)
  • በ”ወሀቢያ” ላይ ቂም የቋጠሩ ልዩ ልዩ የህብረተሰብ ክፍሎችና ታዋቂ ግለሰቦች
  • በአንዳንድ ልማዶቻቸው ገዝፈው የሚታዩ ሰዎች (ለምሳሌ በቤታቸው የ“መውሊድ” ድግስ የሚደግሱ ሰዎች )
  • በቅርብ ጊዜ ወደ ኢስላም የገቡ ሰዎች
  • ወዘተ…
   አህባሽ በሀገራችን ውስጥ በሚያደርገው እንቅስቃሴ በወጣቱ ክፍል ላይ ብዙም አያተኩርም፡፡ እንዲህ የሆነውም ፍላጎቱ ጠፍቶት ሳይሆን የሀገራችን ወጣቶች እርሱ የሚፈልጋቸው አይነት ስላልሆኑ ነው፡፡ ለምሳሌ ወጣቶቻችን በትምህርት ክፍለ ጊዜ “ለምን፤ እንዴት፤ ምክንያቱስ፤” የመሳሰሉ ጥያቄዎችንና “ማስረጃውን ከቁርአንና ከሀዲስ አምጣ” ማለትን ተክነውበታል፡፡ አህባሽ ግን “አሊም የነገረህን ሳትጠራጠር ተቀበል፤ ክርክር አታብዛ” ባይ ነው፡፡ በዚህ የፍራቻ አቋሙ ከወጣቶቻችን ፊት የሚቆምበት ወኔ የለውም፡፡
   በውጪ ሀገራት የሚንቀሳቀሰው አህባሽ ግን በርካታ ወጣቶችን ለመሳብ ችሏል፡፡ የዚህ ምክንያት እንደየሀገሩ ይለያያል፡፡ ለምሳሌ በሰሜን አሜሪካ በርካታ የፈረንጅ ወጣቶች ስለእስልምና ለማወቅ ይፈልጉና ወደ አህባሾች ጀመኣ ይጠጋሉ፡፡ አህባሽም በእስልምና ስም ፍልስፍናውን ያስተምራቸዋል፡፡ በሊባኖስ፤ በሶሪያና በቱርክ ደግሞ ጤናማ የሆነውን እስልምና በሚያስተምሩ ቡድኖች ላይ ከፍተኛ ተጽእኖና ጭቆና ስለሚደረግ ወጣቱ ዘንድ ለመድረስ በጣም ይቸገራሉ፡፡ የተበከለውን እስልምና የሚያስተምሩት አህባሽና ቢጤዎቹ ግን በነጻ ነው የሚንቀሳቀሱት፡፡
የምልመላና የሰበካ ስልቶች
  • አህባሽ ጽንፈኝነቱ እንዳይታወቅበት ከፍተኛ ጥንቃቄ ያደርጋል፡፡ ባለፈው ክፍል የጠቀስኳቸው ጽንፈኛ አባላቱ እንኳ ይህንን ደካማ ጎናቸውን ላለማሳየት በጣም ነው የሚጠነቀቁት፡፡ ለምሳሌ በደንብ ከማያውቁት ሰው ጋር በዲን ጉዳይ አይከራከሩም፡፡ ከሰውዬው ጋር ተከራክረው አስጨናቂ ውጥረት ውስጥ ሲገቡ ደግሞ ራሳቸው የሚያስተምሩትን ነገር እንኳ የሚክዱበት ወቅት አለ፡፡
  • አንጃው ዋነኛ የማስተማሪያ መጽሀፍቱን ለማንም ሰው አይሰጥም፡፡ እነዚህን መጽሀፍት የሚያገኙት አንጃው ሙሉ እምነት የሚጥልባቸው አባላት ናቸው፡፡ ለሌሎች ሰዎች የሚቀርቡት በራሪ ጽሁፎችና በአነስተኛ ገጾች የተዘጋጁ ትንንሽ መጽሀፍት (pocket book የሚባሉት) ናቸው፡፡ (ለምሳሌ በሀረማያው ስልጠና የተበተኑት መጽሀፍት የአንጃውን ድብቅ እምነቶች አያሳዩም፡፡ እነዚያ መጽሀፍት “ፈዲሀቱል ወሀቢያ” (የወሀቢ ጥፋት) እና ከዚህ ጋር የሚመሳሰሉ ርእሶች ነው ያላቸው፡፡) 
  • አንጃው አዲስ ገቢዎችን ለመጥለፍ እንዲመቸው ቱጃሮችንና ታዋቂ ግለሰቦችን ይጠቀማል፡፡
  • የአንጃው አባላት ጓደኞቻቸውን ይጀነጅናሉ፡፡ በዝምድናና በጉርብትና በኩልም ሰዎችን ለመጥለፍ  ይሞክራሉ፡፡ ይህንን የሚያደርጉት ግን ብዙ ኢልም የሌላቸውን ሰዎች እየመረጡ ነው፡፡
  • የአህባሽን መስራች ከልክ በላይ እያገዘፉ ማወደስም ሌላው ዘዴ ነው፡፡ ስለ ሼኽ አብዱላህ ብጹእነት፤ ስለ እውቀታቸው፤ ስለዘር ሀረጋቸው፤ ስለ ከራማቸው ወዘተ… እየተደጋገመ ይጻፋል፤ ይወራል፡፡
  • ትልቁ የፕሮፓጋንዳ ስልታቸው ግን “ወሀቢያን” እንደ ጭራቅ አድርጎ መሳል ነው፡፡ በመሆኑም “ወሀቢ” በሚሉት ቡድንና ኢብን ተይሚያህ፤ ኢብን አብዱል ወሃብ፤ ሰይድ ቁጥብ፤ ኢብን ባዝ ወዘተ… በመሳሰሉ ምሁራን ላይ የማያቋርጥ እርግማን ይወርድባቸዋል፡፡ በቅጥፈት የተፈበረኩ ወሬዎችና ተረቶች ይወራባቸዋል፡፡ ለምሳሌ ከዚህ ቀደም የነገርኳችሁ “የእንግሊዛዊው ሰላይ የጸጸት ማስታወሻ” አህባሾች ለፕሮፓጋንዳ ከሚጠቀሙባቸው ታላላቅ መሳሪያዎች አንዱ ነው፡፡
  • በአለም አቀፍ ደረጃ የሚጠቀሙበት ዋነኛው መሳሪያ ኢንተርኔት ነው፡፡ የኢንተርኔት ገጾችንና ብሎገሮችን በድርጅት ስም ብቻ ሳይሆን በግለሰቦችም ስም ይከፍታሉ፡፡ (በኢንተርኔትም ቢሆን ትልቁ ዘመቻ የሚካሄደው በ“ወሀቢያ” ላይ ነው፡፡)
   አህባሽ ወደ ሀገራችን ከገባ ድፍን አስር አመት ሆኖታል፡፡ በዚህ ቆይታው አስር ሺህ አባላትን እንኳ አላፈራም፡፡ አንድ ሰሞን ረብሻ ለመፍጠር ሞክሮ ሰው “ሆይ ሆይ” ሲለው ድምጹን ወዲያዉኑ ነው ያጠፋው፡፡ አብዛኛው የኢትዮጵያ ህዝብ “አህባሽ” የሚለውን ስም የሰማው ዘንድሮ ነው፡፡ ይህ ቡድን እስከዛሬ ድረስ በሺዎች በሚቆጠሩ ተከታዮቹ ብቻ ተገድቦ የቆየው በምን ተአምር ይሆን?
   ይህ የአላህ ተአምር ነው እላለሁ፡፡ አላህ በጥበቡ ከመርከዝ ውጪ እንዳይሰማ አድርጎታል፡፡ ለወደፊቱም እዚያው ባለበት ያቁምልን! አሚን!!!

No comments:

Post a Comment